Message from General Director

User Rating:  / 3
PoorBest 

ጠንካራ የፖሊሲ ማዕቀፍ ላይ በተመሰረተው የገቢ/የታክስ ስርዓታችን ሀገራችንን ለማሳደግ የሚያስፈልገውን ሀብት ማመንጨት የጋራ ጉዳያችን ነው፡፡ ይህንኑም በአንደኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን አሳክተነዋል::

በክልላችን ሰፊ የሆነ የገቢ አቅም አለ፣ በተገቢው ግን እየሰበሰብን አይደለም፣ ገቢ ካልሰበሰብን ህብረተሰቡ ያነሳቸውን የመልካም አስተዳደርም ሆነ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት አንችልም፡፡

ስለዚህ በየደረጃው የሚገኙ ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ሕዝቡ በተለይ ደግሞ ግብር ከፋዩ ግዴታውን አውቆ ከኛ የተለየ ክትትል ሳያስፈልገው ህጉንና ደንቡን ተከትሎ ግብሩን የሚከፍልበት ሁኔታ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፤ ያኔ አካባቢያችን፣ ከተማችን፣ ክልላችን፣ ሀገራችን በጋራ ልናሳድግና ከራሳችን በሚመነጭ ገቢ ከጥገኝነትና የሌሎች እርዳታ ከመፈለግ ወጥተን በምንፈልገው ደረጃ በመንቀሳቀስ የህዳሴ ጉዟችንን የተሻለ የምናደርግበት ዕድል ይፈጠራል፡፡

 

ስለዚህ በየደረጃው በተቋሙ የምንገኝ አመራሮች፣ ፈጻሚዎች ዙሪያችን ያሉ ባለድርሻ አካላትና በዋናነት ደግሞ ግብር ከፋዩ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል፡፡በሌላ መልኩ የታክስ ስርዓታችን ውጤታማነት ከመንግሥት የወጪ ፍላጐት መሸፈን አንፃር በክልላችን በ2002 ከነበረበት 19 በመቶ በአሁኑ ወቅት 33 በመቶ ላይ ደርሷል፡፡ በገቢ አሰባሰብ ረገድ በ2002 ከነበረበት 944 ሚሊዮን ብር ወደ ብር 5 ቢሊዮን ማድረስ የተቻለ ሲሆን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጨረሻ ብር16 ቢሊዮን በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ግብ ተቀምጧል፡፡ ይህንን እውን ለማድረግም ሁላችንም በጋራ መሥራት አለብን፡፡ የሀገራችንን የልማት ወጪ የሚሸከም የታክስ/የግብር ሥርዓት ለመፍጠር፣ በዚህም ልማታችንን ለማራመድ፣ ብሎም ሌሎች የግብር/የታክስ ሚናዎችን በአግባቡ እንዲወጣ ጠንክረን መሥራት ይገባናል፡፡

 

 

ይህንን ለማድረግ ደግሞ በገቢ ልማት ሠራዊት ግንባታው ላይ የመጀመሪያ ትኩረት ማድረግ ይገባናል፡፡ በገቢ ልማት ሠራዊት የመደራጀቱ ፋይዳም የግብር/የታክስ ሙስናን ለመድፈቅ ዓይነተኛ መሣሪያ አድርጐ ለመጠቀም ነው፡፡ የግብር/የታክስ ህግጋቱ ወደውጭም ሆነ ወደውስጥም የሚሰሩ የመሆናቸውን ጠቀሜታ በሥራ ልንተረጉመው የምንችለው የግብር/የታክስ ህግጋት ጥሰትን በህግጋቱ እርምት የመውሰጃ መንገዶች ልንፈውስ የምንችለው የገቢ ልማት ሠራዊትን እውን አድርገን በአደረጃጀቱ ስንገለገል ብቻ ነው፡፡

 

ከኪራይ ሰብሳቢነት የፀዳ የታክስ ስርዓት ገንብተን ዘመናዊና ተደራሽ አገልግሎት በመስጠት፣ ወደፊት የተራመደች፣ የበለጸገች እና ቀድሞ ከነበረችበት ልዕልና ላይ የተመለሰች ኢትዮጵያን ለመገንባት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ መትጋት ከመላው አመራርና ፈጻሚ ከፍተኛ ቁርጠኝነትና እንቅስቃሴ የሚጠበቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ግብር ከፋይና ባለድርሻ አካላትም የሚጠበቅባቸውን ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ የራሳችንን ልማት በራሳችን ገቢ እውን ከማድረግ ባለፈ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ የሆነበት ልማት ለማረጋገጥ የታክስ ሰርዓቱ የማይተካ ሚና ያለው በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት፡፡

 

ግብር ከፋዮቻችን በታማኝነትና በሃቀኝነት በሚጠበቅባቸው መጠን ግብር በመክፈል እና ታክስ ሰብስቦ በማስገባት ልማታዊነትን በማጠናከር የግብር/የታክስ ልማት ሠራዊት አካል እንድትሆኑ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

 

መላው የክልላችን ማህበረሰብ በግብይት ወቅት ተገቢውን ደረሰኝ በመውሰድ እና በታክስ/በግብር ማጭበርበር ድርጊት ተቃራኒ ሆኖ በመቆም የሀገር ልማት እንዳይደናቀፍ የግብር/የታክስ ልማት ሠራዊቱ አካል እንዲሆንም ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

 

የሀገራችንን ልማት በሀገራችን ገቢ እናሳካለን!

 

አመሰግናለሁ!

 

Thursday the 21st. . Design © Top poker sites - All rights reserved.